המסע אל אג’רה 2 להצלת היהודים: התרגום יבוא בקרוב

יהודי אתיופיה

ጉዞ ወደ ኢጀሬ – 2

ለዘመናት ሥራን ባህሉ ያደረገው የሰሜን ሸዋ ባለእጅ ቤተ – እስራኤል ማህበረሰብ ለአጎራባች ህዝቦች በእጅ ጥበብ ሙያዎች በሽመና፣ ብረታ ብረት፣ በሸክላና በቆዳ ስራዎች ያበረከተው ሰፊ ስራ የሚታወቅ ቢሆንም ሁልጊዜ ሰበ-ነክ ስድቦች፣ የአካል ድብደባ፣ ግድያ፣ የንብረት ውድመትና ስደት ከሚደርሱበት ጥቃቶች ውስጥ ይካተታሉ፡፡ በቅርቡ ህዳር 8/2010 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በፍቼ በኩል ወደ ደራ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢጀሬ ከተማ በግምት የአንድ ሰዓት የእግር ጉዞ በሚገኙ ባለእጅ ማህበረሰብ ላይ የደረሰው ጥቃት ይታወሳል፡፡ 19 ቤቶች፣ 39 ፍየሎች፣ 4 ከብቶች፣ በርካታ ዶሮዎች፣ ንብረቶች፣ ክምር እህል ከነጎተራው፣ ሌሎችም በእሳት ቃጠሎ ዶግ አመድ ሆኗል፡፡[

በሀገሪቱ ለሚደርስ ማንኛውም በሽታና አደጋ እንደ መንስኤና ርኩስ መንፈስ ተሸካሚ የሚታሰቡት መከረኞቹ የያዕቆብ ልጆች ባለእጅ ቤተ እስራኤል በዚህ ዘመን በኢጀሬ ዛፍ ወድቆበት የሞተን ሰዉ “በቡዳ በልታችሁት” ነው የሚልው የጸብ መነሻ ተከትሎ አደጋውን ያደረሱት ሰዎች ድርጊቱን ለፖሊስ ቀርበው ቢያምኑም እስአሁን የመጣ ፍትህ ግን የለም፡፡ የኢትዮጵያ እድገትና ውድቀት ምስጥር የተቋጠረው እዚህ ላይ ነው፡፡ ” የባረኩህንም እባርካለሁ፣ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፡፡” (ዘፍ 12፡3) አንቺ የኩሽ ምድር የበረከቱን ምንጭ ውሃ ማደፍረስሽ ይብቃ፤ ንቂ ንቂ፡፡

አደጋውን እንደሰሙ የሞት ሽረት ሁኔታን በመጋፈጥ ፈጣን ውሳኔ በማድረግ የመጀመሪያውን ሰፊ ዘገባ፣ በምስልና በፊልም መረጃውን አጠናቅረው ለህዝብ ይፋ ያደረጉት መ/ር በላይነህ ታዘብኩና አቶ ተስፋዬ ደሩ ሲሆኑ በቅንብርና በማስተካከል አቶ ሚካኤል ሞገስና ቴዎድሮስ ክብሩ እጅግ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ እንዲሁም መረጃውን ከእነዚህ ሰዎች በመውሰድ አቶ አማንይሁን ረዳ፣ ጋሽ ተክለስላሴ፣ ሌሎችም በመረጃ መረብ በመቀባበል ሰፊ ንቅናቄ ያደረጋችሁ ሁሉ አጥጋቢ ውጤት በድምሩ አስገኝታችኋልና በረከት ለእናንተ ይሁን፡፡

በማረሚያ ቤት መከራ ውስጥ ሆኖ በመላው ኢትዮጵያ በሚደርሱ አስከፊ አደጋዎች ፈጣንና ሰፊ የእርዳታና የድጋፍ እጃቸውን በመዘርጋት የሚታወቁት የተከበሩ ጋሽ ከተማ ከበደ (የኬኬ ኩባንያ ባለቤት) ለኢጀሬ ተጎጂዎች በጠቅላላ 1.2 ሚሊዮን ብር ለቤት መስሪያና የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ እጅግ እናመሰግናለን፤ አምላክ ዘመንዎትን ይባርክ፡፡ ቦታው ድረስ በመሄድና በስልክ የማጽናናትና አለንላችሁ በማለትና የተለያዩ ድግፎችን ያደረጋችሁ የፍቼና ቀጨኔ ቤተሰቦች ሁሉ ህብረታችሁ አኩርቶናል፤ እናመሰግናለን፡፡

በተደጋጋሚ ስልክ በመደወል “ዳግም በህዝቡ ፊት መጥታችሁ እንድታዩን፣ እንድታስተምሩን፣ እንዲሁም ላደረጋችሁት ከፍተኛ ስልታዊ ቅስቀሳ በአካል ልናመሰግናችሁ ስለምንፈልግ ተገኙልን” በማለት ጥሪ በተደረገልን መሰረት በ22/04/10 መ/ር በላይነህ ታዘብኩ፣ አቶ ተስፋዬ ደሩ፣ አቶ ሚካኤል ሞገስና አቶ ቴዎድሮስ ክብሩ ዳግም ወደ ኢጀሬ በመጓዝ ቆራጥ ወንድማማች አጋርነታቸውን ከማሳየታቸውም ባለፈ 84 አባወራዎች በተገኙበት ስብሰባ በማድረግ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዶ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡

 ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች በተደረገላቸው ድጋፍ አማካኝነት የመልሶ መስፈር አስፈላጊነት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ ቦታው ላይ መልሶ መስፈር ፍርሃትና ድንጋጤ የታየባቸው ቢሆንም ህዝቡ አስፈላጊነቱን በግልጽ አስረድቶና በወገኖች የተደረገን የአለንላችሁ ወንድማማችነት ሞራል በመታገዝ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያ ጊዜ መ/ር በላይነህ ቀረጻ ባደረጉበት ወቅት የቀልድ መስሎን ነበር፤ ሆኖም ግን አሁን ይህ ሁሉ ላይ ያደረሰን ያቺ ነገር ነችና ለወገን ተቆርቋሪ መሆን አስፈላጊነቱን ተምረናል በማለት አስተያየት ቀርቧል፡፡

 ጉዳዩ በህግ ተይዞ እልባት ላይ በማድረስ ፍትህ እንዲገኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በተለያዩ የሰሜን ሸዋ ግዛቶችና በኢጀሬ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት በመነሻነት በማንሳት በዘላቂነት ሊሰራ የሚችል ” የባለእጅ ማህበረሰብ ሰብዓዊና ፍትህ ጉዳዮች ክትትል ማህበር” ለማቋቋም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

  የባለእጅ ቤተ እስራኤል ወንድማማችነትና ህብረት ለመፍጠር ታስቦ ስለነበር የሁልጊዜ መገናኛና ጉልበት እንዲሆን በማለት የሰንበቴ ቤት (ሞፈር ቤት) በመመስረት ከአቅራቢያው ካሉ የባለእጅ ገዳማት መሪ አባት ለማምጣት አቋም ተይዟል፡፡

  በቀጣይ በማንነት ዙሪያና ተያያዥ ጉዳዮች በቀጨኔ ከሚገኙ ቤተ እስራኤል ወገኖች ጋር ቅርበት በመፍጠር ደጋፊ የምክክርና ትምህርታዊ ግንኙነት እንዲኖር ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

מה דעתכם על הפוסט?

אתר זה עושה שימוש באקיזמט למניעת הודעות זבל. לחצו כאן כדי ללמוד איך נתוני התגובה שלכם מעובדים.